About The Campaign

ስለእኛ

የትምህርት ሚኒስቴር በአስፈጻሚ አካላት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1263/2014 መሠረት በአጠቃላይና ከፍተኛ ትምህርት ዘርፎች የተዋቀረ ተቋም ሲሆን በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ከ49ሺ በላይ የሚሆኑ የቅድመ አንደኛ፣ የአንደኛ ደረጃ፣ የመካከለኛና የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶችን እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ 47 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን፣ የትምህርትና ሥልጠና ባለስልጣን እና የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎትን የያዘ ነው፡፡

ተግባርና ኃላፊነቶቹም የአጠቃላይና የከፍተኛ ትምህርት፣ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎች፣ ህጎችና እና ፕሮግራሞች መቅረጽ፤ የሥርዓተ-ትምህርት ማዕቀፍ ማዘጋጀት፤ የትምህርት እና የትምህርት ተቋማትን ስታንዳርድ ማውጣት፤ ሀገራዊ የብቃት ማዕቀፍ ማዘጋጀትና በሥራ ላይ መዋሉን ማረጋገጥ፤ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲውን መሠረት መተግበር፤ ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ማዘጋጀትና ጥራትን ማረጋገጥ፣ የፈፃሚን አቅም መገንባትና ክትትልና ድጋፍ ማድረግ፣ ወዘተ. ያካትታል፡፡

 

ስለፖርታሉ

  • በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ከ50 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከ86% በላይ የአንደኛና የመካከለኛ ደረጃ ት/ቤቶች እና ከ71% በላይ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ከደረጃ በታች የሆኑ፣ አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ-ልማት የሌላቸውና ለመማር ማስተማር ሂደቱ ምቹ የሆኑ አይደሉም፡፡ እነዚህን ትምህርት ቤቶች በመንግሥት አቅም ብቻ ለማሻሻል የሚቻል አይደለም፡፡
  • በመሆኑም የትምህርት ቤቶችን መሠረተ-ልማት ለማሻሻል ለሚካሄደው የሕዝብ ንቅናቄ በየደረጃው ያለው ማህበረሰብ፣ ባለሀብቶች፣ ታወቂ ግለሰቦች፣ የቀድሞ ተማሪዎች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ወዘተ. የትምህርት ቤቶችን ችግር በማየት በቀጥታ እገዛ እንዲያደርጉ ለማመቻቸት እንዲቻል ይህ ፖርታል ተዘጋጅቷል፡፡
 

የሕዝብ ንቅናቄው ዋና ዓላማ

  • የትምህርት ጥራት ችግሮች መንስኤዎች ዘርፈ ብዙ ቢሆኑም፤ ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ አለመሆናቸው ከመሰረታዊ ችግሮች አንዱና ዋነኛው ነው። በሀገራችን ከ50ሺ በላይ ከሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ86% በላይ የአንደኛና የመካከለኛ ደረጃ ት/ቤቶች እንዲሁም ከ71% በላይ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ከስታንደርድ በታች ናቸው፡፡ ይህም ትምህርት ቤቶቹ ለመማር ማስተማር አስፈላጊና የተሟሉ  መሠረተ-ልማቶች  ስለሌላቸው ተማሪዎች በተጓደለ የትምህርት ከባቢ ውስጥ እንዲማሩ ተገደዋል። በመሆኑም በየደረጃው ያሉ ተማሪዎች የሚጠበቅባቸውን እውቀት፣ ክህሎትና የባህሪ ለውጥ ማምጣት አለማቻላቸው በግልጽ ታይቷል፡፡
  • ይህን ችግር በመንግሥት አቅም ብቻ ለመፍታት ቢታሰብ ከሶስት አስርት አመታት ያላነሰ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ስለዚህ ይህን ሰፊ ችግር መፍታት የሚቻለው ሥርዓት አበጅቶ በዘላቂነት  የማህበረሰብና የልዩ ልዩ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ማለትም በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ የአካባቢው ማህበረሰብ፣ የቀድሞ ተማሪዎች፤ ታወቂ ግለሰቦች፣ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ባለሀብቶች፣ ወዘተ. በትውልድ ቦታቸው፣ በተማሩበት ቦታ፣ በሚሰሩባቸውና በሚኖሩባቸው አካባቢ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች መሰረተ-ልማቶችን  ማሻሳል ሲቻል ነው፡፡  በመሆኑም እነዚህን ትምህርት ቤቶች በሕዝብ ንቅናቄ አግባብ ለማሻሻል  እቅድ ተዘጋጅቷል፡፡ የዚህ የሕዝብ ንቅናቄው ዋና ዓላማ በየደረጃው ያሉ ማህበረሰብና ልዩ ልዩ አካላትን በማሳተፍ የትምህርት ቤቶችን መሠረተ-ልማት  ለማሻሻል እንዲሁም በዘላቂነት  የመማር ማስተማሩን ሂደቱን በባለቤትነት እንዲደግፍ ለማስቻል ነው፡፡
 

በሀገራዊ ንቅናቄው የሚጠበቁ ውጤቶች 

  • የሕዝብ ንቅናቄ አደረጃጀት በመፍጠር ወደ ተጨባጭ ሥራ መግባት፤ ትምህርት ቤቶችን ማሻሻል፡፡
  • የትምህርት ቤቶችን ነባራ ሁኔታ መለየት፤ እንዲሻሻሉ ማድረግ፡፡
  • በየደረጃው ባለው ማህበረሰብና ልዩ ልዩ አካላት ተሳትፎ የትምህርት ቤቶችን መሠረተ-ልማት  ለማሻሻል የየራሳቸውን ድርሻ በሃላፊነት መወጣት፡፡
  • የትምህርት ቤት መሠረተ-ልማት ለማሻሻል የአሠራር ሥርአት በመዘርጋት በዘላቂነት እንዲቀጥል ማደረግ፡፡
  • ማህበረሰቡና ልዩ ልዩ አካላት በሙያቸው፣ በእውቀታቸውና በጉልበታቸው አስተዋጽኦ ማድረግ፡፡
  • በማህበረሰቡና በልዩ ልዩ አካላት ተሣትፎ የትምህርት ቤቶች መሠረተ-ልማቶች ማሻሻል፡፡